Excerpt for ዉስጥ ሲለወጥ by , available in its entirety at Smashwords


ዉስጥ ሲለወጥ

ራስን የተሻለ ሰዉ የማድረግ

ሚስጥር!!


ተገኘ ምህረት

ብሩክሊን፤ ኒዉ ዮርክ ሲቲጥቅምት 2010 .
ራስህን መለወጥ ትፈልጋለህ? ያለህበት የሩጫ አለም ውስጥ መንገድህ ጠፍቶብሃል? ወከባዉ ከመብዛቱ የተነሳ በራስህ ላይ ያለህ እምነት ወርዷል? ዉስጥህ ደክሟል? መለወጥ ትፈልጋለህ? ዛሬ ካለህበት የተሻለ የኑሮ፣ የአመለካከት፣ የስብእና ደረጃ ላይ መድረስ ትፈልጋለህ? እንግዲያዉስ በምታዉቀዉ፣ በሚገባህ፣ በምትረዳዉና ስሜትህን እስከልብህ ድረስ ገብቶ በሚበረብረዉ የሃገርህ ቋንቋ ያቀረብኩልህን ይቺን ትንሽየ መፅሃፍ አንብብ። ከመፅሃፉ የምታገኘዉ ጥቅም የከፈልከዉን ዋጋ ያህል ካላወጣ እኔ ማተብ የለኝም ማለት ነዉ። አምናለሁ። ይህ መፅሃፍ ህይወትህን የመለወጥ ሃይል አለዉ። ሁሉም ፁሁፎች በፌስቡክ ፔጄ ላይ በተደጋጋሚ ስፅፋቸዉ የነበሩ ሲሆኑ ሁሉም በራሳቸዉ መቆም የሚችሉና ከተፃፉበት ቀን ቅደም ተከተል ዉጪ አንዱ ካቆመበት የመቀጠል አዝማሚያ ስለሌላቸዉ የፈለግነዉ ገፅ ሂደን መጀመር እንችላለን። ጉዳዮቹ ከራስና ከቤተሰብ ጀምረዉ፣ ከመንደርና ከሰፈር ወጥተዉ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሃገራዊ ማንነትን ስለመጠበቅ ያወራሉ። በዚህ ሁሉ መሃከል መሪ ተዋናዩ አንተ ነህ። ፈጣሪዉን ፈርቶ፣ የተፈጠረለትን አላማ የሚወጣ አንድ ጠንካራ ነፍስ ስለመገንባት ስናወራ የፁሁፎቹ ጣት የሚያመለክተዉ ወደ አንተ ነዉ። ይህን አጭር መፅሃፍ ካነበብክ በኋላ ራስህን ቀድሞ ከነበርክበት አለም ወጥቶ እንደምታገኘዉ አልጠራጠርም።

መልካም ንባብ!

ተገኘ ምህረት

ብሩክሊን፤ ኒዉ ዮርክ ሲቲ

ለሰዉ አትኑር። በማንም አትቅና። ለሆድህ አትኑር። ከጥላቻ ራቅ። ሰነፍ አትሁን። ጉረኞችን ሽሽ። ከማይመስሉህ ራቅ። ከዝንጋኤ ተጠበቅ። እያየህ አትሙት። አታጭበርብር። አታስመስል። አትዋሽ። አታባክን። ወላጆችህን ጠብቅ። ስራህን አክብር። ወደላይኞች አትመልከት። ታችኞቹን አትናቅ። የማይሆነዉን አትጠይቅ። ጥቁሩን አትታገል። አትፍረድ። ዋዘኛ አትሁን። ለዉሾች አንገትህን አትድፋ። ለሌቦች አትሳቅ። ለርጉማኖች አታጨብጭብ። እየሳቅህ አትሙት። እየጨፈርክ አትጥፋ። ሞትን አስብ። ድህነትን ቀድስ። ሃብትህን ሸሽግ። ማተብህን ጠብቅ። መንገድክን ጥረግ። ጓደኞችህን ለይ። ዉሎህን መርምር። በአልጋህ አመስግን። ሞሰብህን ባርክ። አትፎካከር። ስለእዉነት አትፈር። የሚሞተዉን አትፍራ። የሚያልፈውን አትደንግጥለት። በተፈጥሮህ ኩራ። በቀለምህ ድመቅ። በማንነትህ አትፈር። እጅህን አትቋጥር። አትንገብገብ። አትኮፈስ። እቡይ አትሁን። ዘር አትቆጥር። የነገሩህን እመን። ያመንከዉን ተቀበል። የተቀበልከዉን አድርግ.... እያልኩ ብዙ መልካም የስብእና መገለጫወችን ልፅፍ እችል ነበር። ነገር ግን ይህ ሁሉ በሁለት ቃላት ሊገለፅ ይችላል። እንዳለመታደል ሆኖ በምእራቡ አለም ሰዶማዉያንና ሃይማኖት አልባዎችም ሳይቀሩ "ፍቅር ያሸንፋል!" በማለት የፍቅርን ዋጋ ከሰማያዊነት አውርደዉ የርኩሰታቸዉ ማጀቢያ ስላደረጉት ይህንን ቃል ለዛሬ ማሰሪያ አድርጌ አልጠቀምም። በምትኩ በየቤታችን ግድግዳ የማይጠፋዉ ባለ ሁለት ቃል ህግ የህግጋት ሁሉ መጨረሻና ማሰሪያ ነዉ። "ፈጣሪህን ፍራ!" ከማንኛዉም የስነ ልቦና ድስኩር ይልቅ ይህ ሰዉን አፍርሶ የመስራትና ወደ ቀናዉ መንገድ የመመለስ ሃይል አለዉ። ይህ ላንተ ምንም ስሜት ካልሰጠህ ወንድሜ መግባትህ አልታወቀህም እንጂ ጭልጥ ያለ የቅዠትና የሰመመን አለም ዉስጥ ነዉ ያለህ። የከፋዉ ደግሞ እንዲህ ለሚሉህ ሰዎች ጆሮህ ከሁለት ሰከንድ በላይ እንኳ ጊዜ የለዉም። በጣም ደካማ ፍጡሮች ነንኮ። ጉንፋን እንኳ በርታ ሲል የሞት ነጋሪት የተጎሰመ የሚመስለን ደካሞች። በራችን እስኪንኳኳ እግራችንን ዘርግተን፣ በየመደሰቻ ቦታዉ እንደስጦ ተሰጥተን እየዋልን ችግርና ድህነት፣ በሽታና ጉስቁልና ከፋ ሲልም ሞት ሲመጣ ያልሰቀልነዉን ፈጣሪ "ና ዉረድ!" የምንል። ምናልባት የህይወታችን ዉሉ ጠፍቶ ከሆነ ቁልፉ ያለዉ እነዚያ ሁለት ቃላት ዉስጥ ይሆናል። ያለ ሙያቸዉ ገብተዉ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን የምን ጊዜም ፈታኝ ጥያቄዎችን በቀላልና ግልፅ በሆኑ ቃላት መግለፅ የቻሉ እንደአቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ያሉ ቅዱሳን አባቶች መልእክትም ይሄዉ ነዉ። ፈጣሪህን ፍራ። "መጀመሪያ የመቀመጫየን!" አለች ዝንጀሮ እንደተባለዉ፣ ሌላዉ ሁሉ ቀስ ብሎ ይደርሳል። ህይወታችን የሚሰክነዉ በእነዚህ ሁለት ዉብ ቃላት ይሆናል። ማንም ቢናገረዉ ይህ እዉነት ከሁለት ሰከንድ በላይ ጊዜ ይፈልጋል። ፈጣሪህን ፍራ!የምናምንበት ሁሉ እንዳለ ሆኖ፤ በአካል፣ በአእምሮ፣ በመንፈስ፣ በስነ ልቦናምና በሃብት ደካማ የሆነ ግለሰብ፣ ማህበረሰብና ህዝብ መጨረሻዉ ረሃብ፣ ስደትና እልቂት ነዉ። የፈጠረን አምላክ ለደካሞች የቆመ አምላክ እንደሆነ እናምናለን። የሚሞቱት ደካሞች፣ የሚኖሩት ደግሞ ጠንካሮች እንደሆኑ እናዉቃለን። እዉቀት ማለት የሚታይ ነዉ። እምነት ደግሞ የማይታይ። እምነታችንን በልባችን እንያዘዉ። በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰዉና እንደህዝብ እንድንኖርና እንድንከበር የሚያደርገን ግን እምነታችን ሳይሆን እዉቀታችን ነዉ። ይህ ሃይማኖትን መቃለል አይደለም። ይህ እዉነታ ነው። ሰማይና ምድርን የፈጠረ አምላክ ከነሙሉ ክብሩ በሚመሰገንባት ሃገር ርሃብና እልቂት፣ ሸርና እርስ በርስ መናናቅና መጠፋፋት ከሞላ፣ ችግሩ ያለዉ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ዉስጥ ነዉ ማለት ነዉ። አይኖቻችን መሬት-መሬት የሚያዩበት ዘመን ይብቃ። ሁሉ ነገራችን ደካማ ሆኖ ያለበት የዉድቀት ዘመን ይብቃ። ሃይላችንና ጊዜያችን፣ ገንዘባችንና ጉልበታችን እኛንም ሆነ ሌሎችን በማይጠቅም ነገር ላይ ማዋሉ ይብቃ። ደካሞች መሆን ይብቃን! ደካማ ማለት ደካማ ነህ ሲሉት የሚያኮርፍ፣ የሚሳደብ፣ የሚናደድ ወይንም በተቃራኒዉ በጣም ደስ የሚለዉ ሰዉ ነዉ። ጠንካራ ማለት ደግሞ ጥንካሬዉን ሲነግሩትም ሆነ ደካማነቱን ሲነግሩት ለሁለቱም ምንም ትርጉም ሳይሰጥ ወደቤት ስራዉ የሚዞር ነዉ። ሺ ታሪክ ይኑርህ፣ ሺ ሃይማኖትና እምነት ይኑርህ፣ ምንም ያህል የተለየ ተሰጥኦ ይኑርህ። ዉስጥህ ደካማ ከሆነ የትም አትደርስም። የከፋዉ ደግሞ ዉስጥህ ጠንካራ ሆኖ እንኳ ዉጪህ ያንን ካልተናገረ ዘመንህን ሙሉ ካለህበት እዉነታ አንድ እርምጃ ሳትራመድ ትኖራለህ። ይህ ዛሬ ላይ ያለንበት እዉነት ነዉ። ምናልባት ትላልቅ የሃገራችን ከተሞች ላይ የምትኖሩ ደንበኞች የምለዉ በቀላሉ ስሜት ይሰጣችሁ ይሆናል። ሺ ዉዳሴ ማርያም ደግሜ ለቃለ መጠይቅ ብገባ ራሴን አረጋግቸና ክብሬን ጠብቄ በእርጋታ ካልተናገርሁ "በጭንቅ አማላጇ ይዠሀለሁ! ይህን ስራ ስጠኝ!" ብለን የፈለግነዉን ልናገኝ አንችልም። ሃይማኖት አምልኮ እንጂ እንጀራና ስራ መፈለጊያ አይሆንህም። ለስብከትህ ካልተከፈለህ በስተቀር። በፀሎት ብቻ ይቺ ሃገር ካለችበት አዘቅት ልትወጣ አትችልም። ፈጣሪን ተስፋ በማድረግ ብቻ ደካማነት ሊወገድ አይችልም። ፈጣሪ እኛ ጠንካሮች እስክንሆን ተስፍ እያደረገ ነዉ ብለን እናስብ። አምልኮታችን እንዳለ ሆኖ ትንሽ ወደምድር የወረደ ነገር ቢኖረን ጉዳት የለዉም። ሁሉንም ነገር "እሱ ያዉቃል!" ብሎ መተዉ ፍፁም የለየለት ስንፍና ነዉ። ጠንካራ መሆን ፈጣሪን መጋፋት አይደለም። ባለህ አቅም ሁሉ ራስክን የተሻለ ቦታ ላይ ለማድረስ መሞከር ሃጢያት ሊሆን አይችልም። ያንተ ደካማ መሆን ሁሉንም ይጠቅማል። ከአንተ ዉጪ። ቤተሰቦችህ ምን ይሆን ይሆን ብለዉ አያስቡም። ምክንያቱም የትም አትሄድም። የተለየ ነገር አታደርግም። ጓደኞችህ ባንተ አይቀኑም። ምክንያቱም ምንም የተለየ ነገር የለህም። ዛሬም እንደትላንቱ ባለህበት ያገኙሃል። መንግስትም ብዙ አይጨነቅም። ምክንያቱም ከእነሱ የተሻለ አስተሳሰብ እንዳለህና ፖሊሲዎቻቸዉን በሙሉ እንደአዲስ እንዲመለከቱ የሚያደርግ ምንም አዲስ ነገር ይዘህ አልመጣህም። በአንተ ደካማነት ማንም ራሱን አይታመምም። ራስ ምታት የምትሆናቸዉ ስትጠነክር ነዉ። ብዙ ሆነዉ ሊገጥሙህ የሚፈልጉት ስትበረታባችውዉ ነዉ። ቤተሰቦችህ አብዝተዉ የሚጨነቁለት ልጅ የሆንከዉ ከእነሱ ርቀህ የምትኖር ጠንካራ ልጅ ስለሆንክ ነዉ። ጠንካራ ሁን ወንድሜ። ለማንም ብለህ ሳይሆን ለራስህና ለሚወዱህ ወላጆችህና ቤተሰቦችህ ስትል። ዉስጥህ መልፈስፈሱን ሊያቆም ይገባል። በከንቱ ተስፋና በዉሸት አለም መኖር ይብቃህ። ተአምር መጠበቁ ይብቃህ። አልጋ ላይ ተኝቶ ፀሎት ብቻ እያደረጉ መኖር ይብቃ። የእዉነት ሰዎች እንሁን። አርሶ እንደሚበላዉ ገበሬ እናስብ። የእዉነት ነዉ የሚኖሩት። በተስፋ ብቻ አይኖሩም። ሁሉንም ነገር ወቅቱን ጠብቀዉ ነዉ የሚያደርጉት። ፍፁም የመነኩሴ አይነት፡ህይወት ለመኖር የሚመች አለም ዉስጥ አይደለም የምንኖረዉ። ፀጋዉን ያደላቸዉ ያንን ህይወት በቤትም በገዳምም ይኑሩት። አንተና እኔ የምንረዳቸዉ ቤተሰቦች አሉብን። የሚራቡና የሚጠሙ ብዙ ነፍሶች አሉብን። ደካማ ሆነን የማችላቸዉ ብዙ ሸክሞች አሉብን። ፈጣሪን "ሸክማችንን ተሸከም!" በማለት ብቻ የማይቀሉ በጣም ብዙ ችግሮች አሉብን። ደካማ ሆነን የማይፈቱ ብዙ ችግሮች። ከንፈር በመምጠጥና ወደሰማይ በማንጋጠጥ በተአምር የማይፈቱ አንድ ሺ አንድ ችግሮች። ደካም አትሁን! ቀና በል! እናም ተራመድ። ደካሞችን የሚያበጥር ዘመን ላይ ነን። መታከሚያ አጥተን እንሞታለን። ራሳችንን ከጠላት መጠበቅ ተስኖን እንወድቃለን። የምንበላዉ አጥተን በጠኔ እናልፋለን። እንጀራ ፍለጋ ወጥተን የአውሬ እራት እንሆናለን። አይ...ደካማ ሆነህ ወጪዉን አትችለዉም ወንድሜ! ሰዎች የሚያዝኑልህ የኔ ቢጤ ምስኪን ሆነህ ኑሮዉን አትችለዉም። ተነስ። ስራ። ጠንካራ ሁን!

አንዳንዶቻችን ከአስተዳደግ ወይንም ከተፈጥሮ ጋር በተገናኘ ሁሌም ሰዎች ስለእኛ የሚያስቡት ነገር ያስጨንቀናል። ልብሴን አልወደዱት ይሆን? አነጋገሬ አስቀይሟቸዉ ይሆን? ትንሽ መስመር ዘልየ ይሆን? ባህሪየ በጣም ተለዉጦባቸዉ ይሆን? ምን ሆኖ ነዉ ዛሬ ሳያናግረኝ የቀረ? ምን ሁና ነዉ ፀጥ ያለችኝ እያልን ራሳችንን የምንበድል ብዙዎች ነን። እንዳንዴ ነገሩ በጣም ገፍቶ የምንኖረዉ ለራሳችን ሳይሆን ለአድማጭ ተመልካች እስኪመስል ድረስ ዉስጣችን ካመነበትና ማንነታችን ከማይወደዉ ነገር ብዙ ርቀን እንሄዳለን። አንድ የምንወደዉ ወይንም የምናከብረዉ ሰዉ ትንሽ ባህሪው ቅይር ካለ የዚህ ጥፋቱ የእኛ እየመሰለን በሃሳብ የምንባዝን ብዙዎች ነን። ስሜቱና ዉሎዉ በአለቃዉ አይንና ግንባር መፈታት ላይ የተመሰረተ ሰውም አይጠፋም። ወይንም አንድ ነገር ፖስት አድርጎ የሚጠብቃቸዉ ሰዎች ላይክ ካላደረጉ ቀኑን ሙሉ ድብር ብሎት የሚዉል ሰው ሞልቷል። ይህ ግን ሙሉ በሙሉ ስህተት ነዉ ባልልም ዉሎ አድሮ ለራሳችን ያለንን ግምትና ለመለወጥ ያለንን ተስፍ ጥያቄ ዉስጥ የሚጨምር መሆኑን ሳልናገር አላልፍም። ሰዎችን አክብር። ይህ ምንም ጥርጥር የለዉም። ተገቢዉን ስራ በትክክለኛዉ መንገድ ፈፅም። ከዚህ በላይ ግን ብዙ አትሂድ። ሰዎች ሁሉ ሁሉን ነገርህን ሊወዱልህ አይችልም። የተወሰኑት ይደግፉሃል። ሌሎቹ ደግሞ ይነቅፉሃል። የትም ብትሄድ ከትችት ስለማታመልጥ በርህን መዝጋቱ የተሻለ አማራጭ ነዉ። ሰዎች ሲያሞግሱህ መዝለልከን ማቆምና ሲያጣጥሉህ ደግሞ ጎሬ ፍለጋ መሄድህን ማቆም አለብህ። እዚህ ጋር "የወፍራም ቆዳን" ነገር ላንሳ። ወፍራም ቆዳ ያላቸዉ ሰዎች እኛ እንደምናስበዉ ይሉኝታ የሌላቸዉና ያፈነገጡ ሰዎች ሳይሆኑ ለራሳቸዉ ያላቸዉን ግምት ለሌሎች ሚዛን አሳልፈዉ የማይሰጡ ጠንካራ ሰዎች ስለሆኑ ነዉ። እዉነት ነዉ በየሄዱበት በትችት መከበብ ጥሩ አይደለም። ግን ደግሞ ይሁንታንና ተወዳጅነትን ለማግኘት ሲባል ፍፁም ከራስ መስመር መዉጣትም ጥሩ አይደለም። ሁሉም በልኩ መሆነ አለበት። ሰዎች ስለሚሉን ነገር መጨነቅ ማቆም አለብን። የምንሰራዉ ስራ በራሳችንና በፈጣሪ ፊት ልክ ነዉ ብለን ካሰብን በስተመጨረሻ ትክክለኛ ፍርድ በሚሰጡ ሰዎች ፊትም ልክ እንሆናለን። ስለዚህ የሚናጋሩትን እንኳ የማያዉቁ ጥቂት ሰዎች ስላደረጉት ወይንም ባለቻቸዉ ትንሽ እዉቀት፥ ገንዘብ፥ ስልጣንና ቁንጅና ተመክተዉ ከደረጃ ሊያወርዱህ በሚፈልጉ ሰዎች ምክንያት የማትወደዉንና የማትፈልገዉን ነገር ማድረግ ያለብህ አይመስለኝም። ሰዎችን ለማስደሰትና "በጣም ጥሩና አሪፍ ልጅ ነዉ" የሚል ስም ለማግኘት ሲሉ በጣም ረጂምና የተሳሳተ መንገድ የሄዱ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ስላሰብኩ ነዉ ይህንን እየፃፍኩ ያለሁት። ለሰዉ ሳይሆን ለራስህና ለህሊናህ ብቻ ኑር። የሰዎች ትችታቸዉም ሆነ ሙገሳቸዉ ለራሳቸው እንዲመች ተደርጎ የሚሰነዘር ነዉ። በጣም የራሴ ከምትለዉ ሰዉ የመጣ ካልሆነ በስተቀር። በአድናቆትና በጭብጨባ ወይንም ትችትን በመፍራት ላይ የተመሰረተ ባህሪ ይቅርብህ!

ሰዎች በፍፁም ደግነትህ የሚያዉቁህ ከሆነ፥ በዉስጥህ ፍፁም ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለ፥ ይህን በማድረግህ ደግሞ በቅርብ የሚያዉቁህ ሰዎች "አበዛኸዉ!" የሚሉህ አይነት መስሎ ከተሰማህ፥ ከሰዎች ይልቅ ለፈጣሪ የምታዳላ ከሆነ፥ ለሰዉ ይምስል የማትኖር ከሆነ፥ ህይወትህ በሙሉ ፀጥታ፥ ርጋታና ቁም ነገር የሞላበት ከሆነ፥ የሰዎች መጥፎነት ታይቶህ የማያዉቅ ከሆነ፥ ሰዎች ሁሉ በፊት ምንም ልዩነት የሌላቸዉ ከሆነ...እግዚአብሔር አንተን ለተሻለ ቦታ መርጦሃል። ማንም ምንም ቢል እንዲህ አይነት ሰዎች በስተመጨረሻ በምድር ላይ በጣም አስፈላጊ የምንላቸዉን ነገሮች ሁሉ ይወርሳሉ። እድሜየ ለዚህ ትንሽ ቢሆኑም በአባቶቻችን እድሜ ያሉ ሰዎችን ቀና ህይወትና ያገኙትን መልካም ነገር እየሰማን ነዉ ያደግን። እንዲህ አይነት ቀና ሰዎች ካላችሁ እባካችሁ ንቀትና እርፍና መገለጫቸዉ በሆኑ ጥቂት ሰዎች ስብእና ምክንያት ከብዙዎቻችን ዘንድ እየራቀ የመጣዉን ደግነትና ፈረሃ እግዚአብሔር ከእጃችን ወጥቶ እንዳይጠፋ እንጠብቀዉ! ወላዲተ አምላክን የምንወዳት አምላክን ሰለወለደች ብቻ የሚመስላቸዉ ብዙዎች ናቸዉ። ይህን ለመናገር ንፅህናየ ባይመጥንም እኛ እሷን የምንወዳት በዉስጥም በዉጪም ፍፁም ሰላም፥ ፍፁም ድንግልና፥ ፍፁም ርህራሄ፥ ፍፁም ትህትና፥ ፍፁም ሃይማኖት ስላላትም ጭምር ነው። ሺ ሳይኮሎጂ ብንማር፥ ሺ ተመስጦ ብትለማመድ፥ ሺ ሙዚቃ ብታዳምጥ፥ የእመቤታችንን እድገትና ህይወት በዚህ አለም እንዴት ሊሆን ይችል ነበር ብሎ ከማሰብ የበለጠ ሊያረጋጋህ የሚችል ነገር የለም። በስተመጨረሻ ሁላችንም ጉልበታችን ይዝላል። አይናችን ይደክማል። እድሜም ይገፋና ወደ ፈጣሪ መጠራት ይመጣል። ያ ሳይሆን በፊት መንገዳችን ይስተካከል። ስለዚህ ወንድሜ፤ ራስን የመለወጥ አንዱ ገፅታ የማይለወጡ ነገሮችን አጥብቆ መያዝንም ይጨምራል። እዚህ ፔጅ ላይ አንዳንድ የበለጠ ጠንካሮች እንድንሆን ከማሰብ የመነጩ የስነ ልቦና ጉዳዮች ቢቀርቡም እነዚህ ነገሮች ሃይማኖትን እስከሞት ከመጠበቅ ጋር የሚጣረሱ እንዳይሆኑ አድርገህ ተረዳቸዉ። የዚህ ፁሁፍ መንፈስ የህይወትህ አብዛኛዉ አካል ከሆነ ፈጣሪ መርቆሃል። ከዚህ ህይወት ርቀህ ከሆነም አሁን ላስታዉስህ። ፈጣሪ የከፉ ነገሮች ሲመጡ ብቻ ሳይሆን የደጉ ጊዜ ላይም ስታገኘዉ ደስ ይለዋል። ጉዳይ ሲኖረዉ ብቻ የሚመጣ ጓደኛ እንደምንጠላዉ ሁሉ ፈጣሪም ሲጨንቀዉ ብቻ የሚመጣን ሰዉ ሁልጊዜም እንደሚያመሰግነዉ ሰዉ የሚያዳምጠዉ አይመስለኝም። እናም የደግነት ፍሬ አንጣ! ራስን መለወጥ ሲባል የማይለወጡ መልካም የሃይማኖት መንገዶችን ጠብቆ መያዝንም ይጨምራል! ፈጣሪ ደግ ሰዉ አያሳጣን!

የሚያናድድ ነገር ገጥሞህ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ያልክበት ቀን ይኖራል ብየ አስባለሁ። ወይንም ደግሞ ሰዎች በጣም የሚያናድድ ነገር አድርገዉህ ዝም በማለትህ ተመልካቾች በአንተ ቦታ ሆነዉ "እንዴት አስቻለህ በናትህ?!" ያሉበት ቀን ካለ ያንን አይንት ቀን ማለቴ ነዉ። ንዴቴን ቀሙኝ ማለት ያልፈለግህበት ቀን። ዛሬ ስለዚህ ስሜት አስፈላጊነት ነዉ ላወራህ የፈለግሁት። ራስህን ከራስህ ነጥለህ ልክ ሌላ ሰዉ እንደሚያይህ ሁሉ አንተ ራስህን ስለመመልከት። ራስን ከራስ መነጠል ብየዋለሁ ለውይይት እንዲመች። ራስን ከራስ መነጠል ሲባል ራስን መርሳት ወይንም ሌላ ሰዉ እንደሆኑ ማሰብ ማለት አይደለም። ወይንም ዛሬ ላይ ስልችት እስኪለን ድረስ ማንነትንና ባህልን፥ ሃይማኖትንና ያደጉበትን ቀየ የማይወክል አይነት ራስን አግዝፎ ማየት ወይንም ፍፁም ሌላ ሰዉ መምሰልም አይደለም። በተቃራኒዉ ራስን ከራስ መነጠል ማለት ራስን ማስታወስ ማለት ነው። ራስን ከራስ ነጥሎ ማየት ማለት ራስን በራስ አይን ማየት፣ እያንዳንዷን ሃሳባችንን፣ ድርጊታችንንና ስሜታችንን ማስታወስ፣ ከአንደበታችን የሚወጣዉን ነገር ኦዲት ማድረግ ማለት ነዉ። ወይንም ነፍስና ስጋ ሲለያዩ ሞት ነዉ ካላላችሁኝ ነፍሳችን ስጋችንን ስትቆጣጠረዉ እንደማለት ነዉ። ይህ ማለት ልክ ዛሬ በጣም ባደጉት ሃገሮች እንደምናየዉ በሁሉም መንገዶች፥ የስራ ቦታዎች፥ የመኖሪያ ቤት መዉጫና መግቢያዎች፥ የመዝናኛ ቦታዎች ሁሉ ካሜራ እንደሚተከለዉና ማንኛዉም አይነት እንቅስቃሴ ከእይታ ዉጪ እንደማይሆነዉ አይነት ማለት ነዉ። ራስን ከራስ ነጥሎ የራስ ተመልካች መሆን ማለት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነዉ። ይህ ሌላ አጀንዳ ያለዉ የስነ ልቦና ጉዳይ አይደለም። ጥርት ያለ ለዉጥ መሰረት ያደረገ ፍልስፍና ነዉ። ለምሳሌ ዉዳሴ ማርያም እየደገምን ነዉ እንበል። እየደገምን መሆኑንም ልብ የማንል ብዙዎች ነን። ልቦናችንን እንሰብስብ፤ በማን ፊት እንደቆምንም ልብ እንበል ሲባል ራሳችንን እንመልከት ማለት ነዉ። ልክ ያንን ስሜት ነዉ ወደህይወታችን ማምጣት ያለብን። አቋቋማችንን፥ ሃሳባችንን፥ ሁሉ ነገራችንን እንደሌላና ከዉጪ እንደቆመ ሰዉ የምንቆጣጠርበት ፍልስፍና። ይህን የህይወት ፍልስፍና መለማመድ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። አንደኛ ነገር ብዙ ስህተቶች የሚሰሩት ራስን ከዉጪ ሆኖ ካለመከታተል ነዉ። ሁለተኛ ራስህን ልክ እንደሌላ ሰው ሆነህ ብትመለከተዉ ልታስተካክለዉ የምትችለው ነገር በጣም ብዙ ነዉ። ሶስተኛ የአብዛኞቹ የታላላቅ ሰዎች የስኬታቸዉ ሚስጥር ይህ ነዉ። ሁሌም ሙሉ ሃሳባቸዉን፥ ስሜታቸዉና አጠቃላይ ሁኔታቸዉን ልብ ይላሉ። ሲራመዱ፥ ሲቀመጡ፥ ሲያወሩ ሁሌም ራሳቸዉን እያዩ ነዉ። አራተኛ አብዛኞቹ የተረጋጉና በራሳቸዉ የሚተማመኑ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ይህንን ነዉ። በደመ ነፍስ አይናገሩም። በደመ ነፍስ ስራ አይሰሩም። በደመ ነፍስ አይበሉም፤ አይጠጡም። እያንዳንዷን እንቅስቃሴያቸዉን ከዉጪ ሰዉ የበለጠ ይከታተላሉ። ለዚያም ነዉ ሲናደዱና ሲደሰቱ በጣም ረጋ ያሉ ሆነዉ የምታያቸዉ። የሚያናድድ ነገር ሲገጥማቸዉ ልክ የተጣሉ ጎረቤቶቹን ከርቀት ሆኖ እንደሚያይ ሰዉ ራሳቸዉን አርቀዉ ነዉ የሚመልከተቱት። ለደስታም ቢሆን ተመሳሳዩን ያደርጋሉ። ይህንን ራስን ከራስ ነጥሎ የመመልክት የህይወት ፍልስፍና ለሚከተል ሰዉ ኑሮ እንዲሁ በዘልማድ የሚደረግ ጉዞ አይሆንም። የረጋና ሰላማዊ መንፈስ ይኖረናል። አንናደድም። አንቀናም። አንደናገጥም። ብዙ ስህተት አንሰራም። ሰዎች አይንቁንም። ራሳችንን አናዋርድም። ብዙ ዉስጣዊ ጥቅሞች ይኖሩታል። የሰጠሁት ስያሜና አጠቃላይ ነገሩ ግራ የሚያጋባና እንግዳ መስሎ ከተሰማህ ይህን ብቻ እንድታደርግ እመክራለሁ። ለተወሰኑ ጊዜያት እያንዳንዱን ስሜትህንና ሃሳብህን ልክ እንደጎብኚ ተከተለዉ። ምንም አታድርግ። እንዲሁ አእምሮህና አካልህ ያለበት ቦታ ላይ አንተም እዚያዉ ተገኝ። አብረኸዉ ዘወር-ዘወር በል። ልብ በል እእምሮ ስሙ አንድ ይሁን እንጂ ብዛቱ አይታወቅም። ታስባለህ። እያሰብክ መሆኑንም ታስባለህ። ይህንንም ታስባለህ። ልክ አንድ እንደኮምፒዉተር አንድ ዊንዶ ከፍተህ ሌሎች ብዙዎችንም እንደምትከፍተዉ ማለት ነዉ። ይህንን እዉነት ለራስህ በሚጠቅም መልኩ ስለመጠቀም ነዉ ይህ የስነ ልቦና ፍልስፍና የሚያወራዉ። ለተወሰኑ ቀናት ይህንን ለማድረግ ሞክር። ልብ በል። ቴዲ አፍሮ ለኢንተርቪዉ ሲቀርብ መልሱን ብቻ አይደለም ይዞ የሚመጣዉ። ራሱን፥ ሃሳቡን፥ ድምፁን፥ የእጅና የእግር አቀማመጡን፥ የፊት ስሜቱን ሁሉ አዘጋጅቶ ይዞና ተቆጣጥሮ ነዉ የሚቀርበዉ። ያ ማለት እንደሌሎቹ መልስ ለመመለስ ከመጣደፍ ይልቅ በእያንዳንዷ ቅፅበት ከራሱ ጋር ስለመሆኑ ይበልጥ ይጨነቃል ማለት ነዉ። ለዚያ ነዉ ብዙ ጊዜ ነገሮችን በጥድፊያ፥ ወይንም በዘፈቀደ ሲያደርግ የማናየዉ። እያንዳንዱ እንቅስቃሴዉ በራሱ እይታ ዉስጥ ነዉ። ስነ ልቦና (ስነ ባህሪ በሚለዉ ብዙም ስለማልስማማ ነዉ) እስካልሞከርከዉ ድረስ ሊሰራልህ አይችልም። ይህንን ካልሞከርከዉ ጥቅሙና ምንነቱ ላይገባህ ይችላል። ራስክን የተሻለ ስብእና ያለዉ ሰዉ ለማድረግ ፍላጎቱ ከሌላህም ብዙ አልጫንህም። ግን በዚህ ርግጠኛ ሁን። እንደአብዛኛዉ ሰዉ ራስህን ረስተህ የምትኖር ከሆነ ልክ እንደአብዛኛዉ ሰዉ አይነት ህይወት ነዉ የምትመራዉ። መለወጥ ካለብህ ራስህን ከራስህ ነጥለህ ሁሉ ነገርህን መከታተልና ሊስተካከሉ የሚገባቸዉ ነገሮች ላይ ልትሰራ ይገባል ብየ አምናለሁ። አንድ ሰዉ ሲለወጥ ምድር ትለወጣለች! መልካም ቀን! /ማርያም ብሩክሊን፤ ኒው ዮርክ (የዚህ ፍልስፍና መነሻ የምስራቁ አለም የሃይማኖት መንገዶች ናቸዉ ተብሎ ይታመናል። ሌላ ብዙ ዘባተሎም ይኖረዋል። ነገር ግን የእኛ ተፈጥሮ ከኢትዮጵያ እንጂ ከምስራቅ ስላልመጣ ለእኛ በሚመችና መንፈሳዊም ሆነ ምድራዊ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መልኩ መጠቀም ጉዳት የለዉም።)

ኑሮ ፍትሃዊ አይደለም። አንድ ቤት ዉስጥ ቁንጅና፣ ሃብት፣ ዝና፣ ፅኑ ሃይማኖትና እዉቀት ሞልቶ ታያለህ። ከአንዳንዶቻችን ቤት ደግሞ ድህነትና ድንቁርና ፈጣሪን ከማማረር ጋር ሞልቶ ታያለህ። አንድ ሰዉ ላይ ሁሉም የፈጣሪ እርግማን የወረደበት እስኪመስለን ድረስ በብዙ መልኩ የተበደለ ሰው እናያለን። የነገን ማንም ባያዉቅም ተስፋ እንኳ ያለዉ መሆኑን የምንጠራጠረዉ ብዙ ሰዉ አለ። ነገር ግን በአንድ ነገር እርግጠኛ እንሁን። ከድንገተኛና ከተፈጥሮ አደጋዎች ዉጪ እኛ ላይ የሚደርሰዉ እያንዳንዱ ዉድቀትና ድንቁርና ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የራሳችን የእጅ ስራ ዉጤት ነዉ። ዛሬ ላለህበት ሁለንተናዊ ሁኔታ ከአንተ ዉጪ ሌላ ማንኛዉንም አካል ተጠያቂ ካደረግክ ለራስህ ጉድጓድ መቆፈረህ ሳያንስ ራስክን ትቀብራለህ። ለማንም ብየ አይደለም ይህን የምልህ። አንተ የራስህን ህይወት መሸከም ካልቻልክ ማን ሊሸከምህ ይችላል? አንተ ለእያንዳንዱ የህይወት ገጠመኝህ ሃላፊነት ካልወሰድክ ማን ሊወስድልህ ይችላል? አንድ ቤት ዉስጥ ከሃብት እስከእምነት፣ ከእዉቀት እስከቁንጅና ተጠቃሎ ሲገባ አንተ ቤት ዉስጥ ግን ከነዚህ ዉስጥ አንዱም እንደሌለ ስታስብ ምን ታስባለህ? ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዉ ማን ይመስልሃል? ፈጣሪ? መንግስት? ጎረቤቶችህ? ጓደኞችህ? የአርባ ቀን እድላቸዉ? ድግምት? ይህ ሁሉ ለአንተ ምን ይጠቅምሃል? የቤትህና የህይወትህን ቁልፍ ከሌላ ሰው ኪስ ዉስጥ አታገኘዉም። ደግሜ እልሃለሁም ዛሬ ላለህባት እያንዳንዷ እዉነት ከአንተ ዉጪ ሌላ ማንም ሃላፊነት አይወስድም። ይህን የምልህ ህሊና የሌለኝ አንድ አንጀት ሆኜ ሳይሆን እንደ ሰዉ፣ አንድ ህሊና እንዳለዉ ሰዉ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የወደፊት ተስፋ አይኔ ላይ ሲመክን እያየሁ ስለምፈራ ነዉ። ይቺ ሃገርኮ እግዚአብሔር በየቦታዉ ስላስቀራቸዉ መልካም ቤተሰቦች ባይሆን ኖሮ ዛሬ የለችም ነበር። እነዚህን ቤተሰቦች በሜዲያ አታያቸዉም። ድምፃቸዉንም አትሰማም። ግን ልጆቻቸዉ ትላልቆች ናቸዉ። ቆንጆዎች ናቸዉ። ለማተባቸዉ ይሞታሉ። ስለሃይማኖታቸዉ ይደማሉ። በጣም ሃብታሞች ናቸዉ። ዝናቸዉን የሚያቁት በጉርብትና የሚያዉቋቸዉ ናቸዉ። ሃገሪቱን የሚያገለግሉት ከላይ እያስጨበጨቡ ሳይሆን ከስር እየተነጠፉ ነዉ። እነዚህን ቤተሰቦች ባየህበት አይን ራስህን እንድታየዉ ነዉ ፍላጎቴ። ሁሉንም መልካም ነገር ይዘዋል። ሁሉንም። አንተና እኔ ደግሞ በተቃራኒዉ ምንም የለንም። ምንም። ሃይማኖቱ፣ ጥንካሬዉ፣ ግርማ ሞገሱ፣ እዉቀቱ፣ ማስተዋሉ። ሁሉም የለንም። ምክንያቱም.... ምክንያቱም አንተና እኔ አናስብም። አንተንና እኔን ከእነሱ የሚለየን አለማሰባችን ነዉ። የህይወታችን ዉሉ ያለዉ ከአለቆቻችን፣ ከደመወዛችን፣ ከቤተሰቦቻችን፣ ከመንግስት ወይንም ከጓደኞቻችን ላይ ሳይሆን ራሳችን አእምሮ ዉስጥ መሆኑን አለማሰባችን ነዉ ትልቁ ድክመታችና እንዳንገናኝ አድርጎ ያራራቀን። አሁንም አልረፈደም ወንድሜ! ሰበብ መደርደርህን ተዉ። ማማረርህን አቁም። ከአንተ ዉጪ ባለ በማንኛዉም ነገር ላይ ተስፋ ማድረግህን አቁም። ሰዎችን ጥፋተኛ አታድርግ። አንድ ጥፋተኛ ሰዉ ቢኖር አንተ ብቻ ነህ። የመዉቀስ ሱስ ኖሮብኝ ሳይሆን አንተ እንድትለወጥ ከተፈለገ አቋራጩና ትክክለኛዉ መንገድ ይህ ነዉ። ልናድግ ግድ ይለናል። በጣም ጠንካሮች ልንሆን ይገባል። ደካማ መሆን ማንንም አይጠቅምም። የሚጠቀም አካል ካለም ደካማ መሆንህ የሚጠቅመዉ ሌሎችን ነዉ። ይህንን አቁም። ሃላፊነት ዉሰድ። በሰዎች ላይ የምትጥለዉን ተስፋ የመጨረሻ አማራጭ አድርገህ ዉሰደዉ። እናም አስብ። ድህነትና ድንቁርና አንድ ቤት ዉስጥ መኖር የለባቸዉም። በዚሁ ላይ ደግሞ ክህደትና ስንፍና ጨምረን መጨረሻችን ለሰሚም ግራ ነዉ የሚሆን። ተነስ። ከተኛህበት ተነስ። ከንቱ ተስፋህን ጣል። እጆችህና እግሮችህ ይንቀሳቀሱ። አእምሮህ ይስራ። ለራስህ ቃል ግባ። ፋፁም ከትላንትናዉ የተሻልክና ለራሱ ህይወት ሙሉ ሃላፊነት የሚወስድ ሰዉ ሁን! መልካም ቀን! ላለንበት ችግር ሁሉ ከራሳችን ዉጪ ያሉ አካላትን ተጠያቂ የምናደርግበት ዘመን ይብቃ!

ህልም ካለህ ጊዜዉ ገና ነዉ። ለምንም ነገር ቢሆን ጊዜዉ አልረፈደም። ካለፈዉ ዘመን ይልቅ ወደፊት ያለዉ በጣም ዉድና አስፈላጊ ነዉ። ትላንት በሰራኸዉ ላይ ተንተርሰህ ከምትኖር ዛሬ በቀለስከዉ መንገድ ላይ ስትጓዝ ብታረጅ የበለጠ ደስታና ስኬት አለ። ሁሌም ዉስጣችን እንደልጅ ይሁን። ልባችን የማይሞት ነገ አድጌ የበለጠ ስራ ሰርቸ ራሴንና ቤተሰቦቸን ለዉጨ እያልን የምንኖር ዉስጣችን የማይሞት ህፃናት እንሁን። ገና በሃያና በሃያ አንድ አመታችን የቀለስነዉ ያልበሰለዉ የህይወት መንገዳችን የቀሪ ዘመናችን ፍፃሜ እንዲሆን አንፍቀድ። ዛሬም ቀሪ ዘመንህን የተሻለ የሚያደርግ ዉሳኔ መወሰን ትችላለህ።

አዲሱ አመት ለራስህ ህይወት ሃላፊነት የምትወስድበት፥ እንደሰው በሁለት እግርህ የምትቆምበት፥ ከከንቱ ተስፋ ርቀህ እጆችህ በስራ የሚዝሉበት፥ ያቋረጥከዉንና የናቅከዉን ትምህርት የምትቀጥልበት፥ ቂም ከመቆጠርና ብቀላ ከማሰብ ወጥተህ ህይወትህን በተሻለ መንገድ የምትመራበት፥ በጣም ትንሽ ቢሆንም በየወሩም ሆነ በየሳምንቱ ከምታገኘዉ ገቢ ላይ እየቆጠብክ ለነገ የሚሆን ጥሪት የምትይዝበት፥ ራስክን ከማዋረድና ዝቅ ከማድረግ የምትርቅበት፥ በራስህ ላይ ጦርነት ከማወጅ ወጥተህ ሰላም የምትፈጥርበት፥ ስለዚህና ስለዚያ ከማዉራት ወጥተህ አንተንና በዙሪያህ ያሉ ሰዎችን የሚጠቅምና በህይወትህ ላይ ተጨባጭ ለዉጥ በሚያመጡ ነገሮች ላይ የምታተኩርበት፥ ሰዉን በሰዉነቱ እንጂ በስኬቱ የማትለካበት፥ ፈጣሪህን ስለአምላክነቱ ብቻ እንጂ ስላደረገልህ መልካም ነገር ስትል ብቻ የማታመሰግንበት፥ ጎጂ የሆኑ ልማዶችህን አንድ በአንድ ከራስህ ነጥለህ የምታወጣበት፥....ይህንን ፔጅም በቋሚነት የምትከታተልበትና ራስክን የምትለዉጥበት ዘመን ይሁንልህ!

ለራሴ የፃፍኩት ለእናንተም የሚጠቅም ከሆነ -------+++++++++--------- ከድካምህ ብዛት የተነሳ እንቅልፍህ የሞት ያህል ይከብድሃል። ከመዛልህ የተነሳ አርብና እረቡ ራሱ ትዝ አይልህም። ከመድከምህ የተነሳ ልክ የሆነዉና ያልሆነዉ እንኳ ከህሊናህ ጠፍቷል። ደግመዉ ደጋግመዉ ከመስበካቸዉ የተነሳ ሊሞቱ ወራት የቀራቸዉን የካንሰር ህሙማት እንኳ ከእግዚአብሔር መንገድ ይልቅ ወደ ከንቱ ደስታ ሲመሯቸዉ ስታይ እንኳ ልክ ይመስልሃል። እዉነትን ምቾትና ሃብት የሚያብራሩት ይመስልሃል። ዉበትና እዉቀት ሃቅን የያዙ ይመስልሃል። ቆሻሻና ድሃ የሆነ ህዝብ እዉነትና ክብር ያለዉ መሆኑን ትዘነጋለህ። በምድር ሁሉ ያለ ምቾት እስከእድሜ ልክ ቢቀርብላቸዉ እንኳ ማተባቸዉን ከአንገታቸዉ የማይለዩ ዝም ያሉ ሚሊየን ወንድሞች እንዳሉህ ትዘነጋለህ። ባይናገሩም፥ ባይጮሁም፥ ባይለፈልፉም ለክፉ ቀን በነፍስህ እንኳ የምትተማመንባቸዉ የእናትህ ልጆች እንዳሉ ትዘነጋለህ። በየቤቱ በመንፈቀ ሌሊት ነቅቶ ስለሃይማኖቱና ስለእናት ሃገሩ የሚያለቀስ ዉጩ ተራ የሚመስል እንደሰደደ የሚነድ እሳት አዝሎ የሚዞር ወንድም እንዳለህ ትዘነጋለህ። ሺ ቢያፈርሷቸዉ፥ ሺ ቢንዷቸዉ እንደቅዱስ ጊወርጊስ ለህሊና የሚያስቸግር ብርታት ያላቸዉና በተቆረጡት ቁጥር የሚተኩ ሚሊየኖች እንዳሉ ትዘነጋለህ። ስለእነዚህ ሚሊየኖች ስትል ሃሳባቸዉና ድርጊታቸዉ ሁሉ ከረከሱት ሰዎች ራቅ። በማንም ላይ ተንኮል አታስብ። የሚሰማህን ነገር ለሚመለከተዉ ሰዉ ተናገር። ሃይማኖትህንና የሚጠቅምህን የአባቶችህን ባህል በማተብህ ምለህ ያዝ። ከእዉነትና ከፈጣሪ ዉጪ ሌላ ዳኛ አይኑርህ። ድካምህን አስብ። ስንፍናህን ልብ በል። ለአንድ ቀን እንኳ ነቅተህ መቆየት የማትችል አቅመ ቢስ መሆንህን ልብ እያልክ ኑር። ሞት ሃይልና ጥበብ ነዉ። ሞቱን የሚያስብ መልካም ሰዉ ነዉ። ከፊት ለፊቱ የሚያየዉና የሚያዋራዉ ሰዉ በማንኛዉም ሰአት የሚሞት መሆኑን የሚያስብ ሰዉ አስተዋይ ነዉ። ስለሚያልፉ ነገሮች ከሚያልፍ ሰዉ ጋር አይከራከርም። ደግሞስ በአቅምህ ማድረግ ያለብህን ታደርጋለህ ወይንስ ለምትወደዉ ስታጨበጭብና የጠላኸዉን ደግሞ ስታወግዝ ትኖራለህ? ስማኝ ልንገርህ ተገኘ! በራቸዉን ዘግተዉ፥ አንደበታቸዉን ዘግተዉ ለሃገራቸዉና ለህይማኖታቸዉ ስለሚደሙ ዉድ እህትና ወንድሞች ስትል አንተም የድርሻህን ተወጣ! በስተመጨረሻ መልካምና ቀና ሰዎች ያሸንፋሉ። የተንኮል፥ የሴራና የመሰሪነት መጨረሻዉ ሟሙቶ ማለቅ ነዉ። መቸና እንዴት እንደጠፉ እንኳ አታዉቅም። እናም ደስ እያለህ መቃብር አትዉደቅ። እግዚአብሔር የሌለበት እያንዳንዱ ደስታ የዘመናችን የስኳር ምግቦችን ያህል ዉሎ አድሮ ጉድ ያመጣል። ደስ እያለህ የምታደርጋቸዉ ምድራዊ ነገሮች ሁሉ መጨረሻቸዉ ጥድፊያ ነዉ። ለሞት፥ ለዉርደት፥ ለዉድቀት፥ ለክስረት፥ ለወንጀል ጥድፊያ። ለእነዚህ ነዉ የምንጣደፈዉ። ወጥ የሚጣፍጠው በሚከነክነዉ በርበሬ ወይንም በሚመረዉ ጨዉ እንጂ ማር-ማር በሚለዉ ስኳር አይደለም። የፈጣሪ መንገዶች እንደጨዉ መረዉህ ወይንም እንደመርግ የከበዱህ መስሎህ ይሆናል። ምናልባት ህግጋቶቹ ከምድሩ ህይወት ለይቶህ ይሆናል። ከሚታየዉ ደስታም ተካፋይ እንዳትሆን አድርጎህ ይሆናል። ሰዎች ዝምታህ አስፈርቷቸዉ ሸሽተዉህም ይሆናል። ህሊናህ አንዴ እዚህ አንዴ እዚያ እያለ አስቸግሮህም ይሆናል። ነገር ግን ከሞት በኋላ ለፍርድ ይዘውት የሚቀርቡት ቅድስና የማያስጨንቁት በዋል ፍሰስ ከመሆን ምድራዊ ፈንጠዝያዉ ሁሉ ጥንቅር ብሎ ቢቀር አይሻልህም? ደግሞስ ሰዉ ከሃይማኖቱና ከፈጣሪዉ የተለየ ህይወት እንዴት ሊኖር ይችላል? ሰዎች አንተን ወደዉ አምልኮህን የሚጠሉ ከሆነ አንተንም አይወዱህም። የሚወዱህ ከሆነ አምልኮህንና መላ ተፈጥሮህን ይቀበላሉ። ድክመትህን ጨምሮ። ድክመት ሰዉ መሆንህን የሚያመለክት ጊዜያዊ ነገር እንጂ ሌላ አይደለምና ራስህን ጨርሰህ አትርሳዉ። ዞሮ ዞሮ ወደቤት ከመመለስ በላይ ምንም ነገር የለም። ስራህ የትም ቢወስድህ፥ ከማትፈልገዉና ከማይመስልህ ሰዉ ጋር ቢያዉልህም ልብህና ቤትህ ግን ያንተ ነዉ። እናም እነዚህን አክብር። ለፈጣሪ ስጥ። ለታይታ ሳይሆን የእዉነት ቅዱስ ቦታዎች አድርጋቸዉ። ቤት ዘግተው ስለሚበስሉ፥ በዝምታ ዉስጥ ስለሚያድጉ፥ ስለሃገራቸዉ ለሚደሙ፥ ከተንኮልና ከሴራ ርቀዉ ለሚያነቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆችና በሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ዉስጥ ላሉ ደጋግ ሰዎች ስትል ከቀናዉ መንገድ አትራቅ! በስተመጨረሻ ደጋግ ትጉሃን ህዝቦች ምድርን ይወርሳሉ! እባክህን ቢያንስ አልፎ-አልፎ ቢሆንም የቅድስናን ህይወት በአቅምህ ልክ ተናገር! ምናልባት አንተ ከሌሎች እንደምትማረዉ ሁሉ ሌሎችም አንተ ከምትናገረዉ ይማሩ ይሆናል!

በምድር ላይ ጊዜና ስራ የማይለዉጠዉ ነገር የለም። እያንዳንዱን ድክመታችንን ጊዜ ይሽረዋል። ነገር ግን ስራ ከታከለበት ፈጥነን እንሽረዋለን። ህልማችን እዉን ይሆናል። ይዘገይ ይሆናል እንጂ በልጅነት አእምሯችን የሳልነዉ አብዛኛዉ ነገር የመሳካት እድሉ በጣም ሰፊ ነዉ። አንተ ወደህልምህ ለመድረስ በስራ ከተጠመድክ ደግሞ የበለጠ ትፈጥናለህ። አንተ እንደግለሰብ ያሉብህን ድክመቶች ለመፍታት አእምሮህና እጅህ በሰራ ቁጥር አንተም ፈጣሪህን ትረዳዋለህ። ፈጣሪን የምንረዳዉ ራሳችንን በመርዳት ነዉ። ፈጣሪያቸዉን የሚረዱት ራሳቸዉን የሚረዱት ናቸዉ። ፈጣሪን የሚያማርር ህዝብ የበዛባት ሃገር ብዙ ራሳቸዉን መርዳት የማይችሉ ህዝቦች ያሉበት ሃገር ነዉ። ፈጣሪን "ምን በድየህ ነዉ እንዲህ ያደረከኝ!" እያልን ፀሎትና እሮሮ ከምንቀላቅል ያለችንን ይዘን ወደስራ ብንመለስ እሱም ደስ ይለዋል። ሃይማኖታችንም አይሰደብም። እኛም ጠንካሮች እንሆናለን። በስነ ልቦና ደካማ የሆነ ህዝብና የራሱን ሸክም ለመሸከም ያልተዘጋጀ ማህበረሰብ ፈጣሪን አይረዳዉም። ፈጣሪ እርዳታ የሚያስፈልገዉ ሆኖ አይደለም ይህንን የምለዉ። በራስህ ድክመት ላመጣኸዉ ችግርና መከራ ሁሉ ፈጣሪና ሃይማኖትህ ይሰደባል። ልክ ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት ሁለንተናዊ ችግር ሁሉ ዜጎቿ መጠየቅ ሲገባቸዉ ሃይማኖታችንና እምነታችን ሲወቀስ እንደምናየዉ ማለት ነዉ። ሌሎቹን እንርሳቸዉና አንተን ብቻ እናስብ። ትላንት ከነበርክበት ወደተሻለ ቦታ የሚወስድህ መንገድ ላይ ነህ? ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ አሳልፈህ ሰጥተህ "እንደፈለገ ያድርገዉ!" ብለህ ትተኸዋል? ወይንስ በአቅምህ ማድረግ ያለብህን እያደረግክ ፈጣሪ ሲረዳህ አንተም እየረዳኸዉ ነዉ? የደጉ ዘመን ላይመለስ አልፏል። በሳምንት ሲመችን ብቻ ሰርተን ሌላዉን ጊዜ በጨዋታ የምናሳልፍበት ጊዜ አይደለም። ብዙ መክፈል ያለብህ እዳ አለ። ልትረዳቸዉ የሚገባቸዉ የቤተሰብ አባላትና ሰዎች ይኖራሉ። በጊዜ መድረስ ያለባቸዉ ብዙ ጓዳዮች ይኖራሉ። ይህ ሁሉ ጊዜዉ መለወጡንና የአንተም አስተሳሰብ አብሮ መለወጥ እንዳለበት ያመላክታል ብየ አስባለሁ። እናም ስራ ስራ። ድክመቶችህ ላይ አተኩር። የምትፈራቸውንና ጠቃሚ እንደሆኑ የምታዉቃቸዉን ነገሮች ተማር። መፅሃፍት ጥሩ ቢሆኑም ከመምህር ጋር በአካል እየተያዩ ፊት ለፊት መማርን የመሰለ ነገር ግን የለም። ስንፍናን ልትጠላው ይገባል። ተሳዳቢ፥ ዘረኛ፥ ሴረኛ፥ ከልክ ያለፈ ቀልደኛ ሰዉ ባለበት ሁሉ ልክ የሌለዉ ስንፍና አለ። ህሊና የሌላቸዉ የሚመስሉ ብዙ ሰዎች የራሳቸዉ ስንፍና ዉጤት ናቸዉ። ይህ ሁሉ ምክንያት ለስራ እንድንበረታ ሊያደርገን ይገባል። ሌላው ሁሉ ቢቀር ከልብህ የምትሰራ ሰዉ ከሆንክ እንቅልፍ እምቢ አለኝ አትልም። ስራ እንስራ! ራሳችንን እንለዉጥ! ፈጣሪን ራሳችንን በመርዳት እንርዳዉ!

ምድር ላይ ሁለቴ አትኖርም። ሁለተኛ እድል የሚባል ነገር የለም። በድህነት ኖረህ በድህነት ብትሞት ድጋሚ ተወልደህ እንደንጉስ ልጅ የፈለግከዉን ባሻህ ሰአት አግኝተህ በደስታ የምታልፍበት ሁለተኛ እድል የለህም። ወይ በአግባቡና በስርአቱ ከነክብርህ ትኖራለህ ወይንም ደግሞ ባለቤት እንደሌለዉ ዉሻ ያየህ ሁሉ ድንጋይ የሚወረዉርብህና እንዲሁ በደመ ነፍስ ስትሮጥ የምትኖር ትሆናለህ። እናም ወንድሜ ቆም ብለህ አስብ። ለማን ነዉ የምትኖረዉ? ምን ስታደርግ ነዉ ጊዜህ የሚመሸዉ? ዝናና ሃብት ላጨማለቃቸዉ ሰዎች ተጨማሪ ደስታ በመፍጠር ላይ ነህ? ወይንስ መፈጠርክን እንኳ ለማያስታዉሱህ ካንተ የተሻለ ቦታ ላይ ላሉ ሰዎች ባማጨብጨብ ላይ ነህ? የሰዎችን ድንቅ ስራና ጥበብ በማድነቅ ነዉ ጊዜህ የሚያልፈዉ ወይንስ የሌሎችን ሰዎች አስደማሚና ህልም የሚመስል ህይወት በመስማትና በማየት ነዉ ጊዜህ የሚያልፈዉ? እንደዚህ እንደምንኖር ሁላችንም እናዉቃለን። ለራሳችን ኑረን አናዉቅም። ጊዜያችንን በሙሉ የሌሎች ሰዎች ጉዳይ ነዉ የሚይዘዉ። ስለራሳችን ማሰብ ያስፈራናል። አንዳንዴ ስለራስ ማሰብ ራስ ወዳድነት የሚመስለንም አለን። እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? ነገ የምትሞት ቢሆን ዛሬ እያስጨነቀህ ያለዉ ነገር በሙሉ ትርጉም የሚኖረዉ ይመስልሃል?! እንዴት አንድ ሰዉ በዚህ ምድር ላይ ያለውን ብቸኛዉን አስፈላጊ ሰዉ ይረሳል? አለም ማለትኮ አንተ ማሰብ እስከቻልካት ጥግ ድረስ ብቻ ነች። ምንም አለም ሰፊ ብትሆን የኖርነዉን ዘመን ስናስበዉ የምናስታዉሰዉ የምናዉቀዉንና የምናምንበትን ነገር ብቻ ነዉ። ታዲያ አንተ እንዴት ራስህን ትረሳለህ። የሚኮንንህም የሚያፀድቅህም፥ የሚያስከብርህም የሚያዋርድህም፥ የሚያነሳህም የሚጥልህም፥ የሚገድልህም የሚያድንህም አንድ ሰዉ ቢኖር አንተ ብቻ ነህ። በዚህ ምድር ላይ በአንተ ላይ ፍፁም ሃይልና መብት ያለዉ አንድ ፍጥር ቢኖር አንድ አንተ ብቻ ነህ። ያለፍላጎትህና ያለአንተ ፍቃድ በራስህ ላይ የሚሆን አንዳች ነገር የለም። ዉሎ አድሮ፥ ተጠራቅሞ ልብ አላልከዉ እንደሁ እንጂ ዛሬ ላይ ላለህበት እያንዳንዱ ነባራዊ ሁኔታ ያንተ እጅ አለበት። ዛሬ የምትኖርበትን ቦታ መርጠህ ነዉ። ስራህ በምርጫህ ነዉ። ትዳርህም የራስህ ምርጫ ዉጤት ነው። ሌላዉ ሁሉ ቢቀር ሰዎች አንተን የሚያቁበት ባህሪህ የራስህ የእጅ ስራ ዉጤት ነዉ። ይህም ማለት ለራስህ ጊዜ ባልሰጠህ ቁጥር፥ ህይወትህን በሙሉ የሌሎች ሰዎች ጉዳይ በያዘዉ ቁጥር አንተ በደመ ነፍስ እየኖርክ ነዉ ማለት ነዉ። የምታደርገዉን፥ የምትናገረዉን፥ የምታስበዉን፥ የሚሰማህን፥ የፊት ገፅታህን፥ አቋቋምህን፥ አለባበስህን፥ ሰላምታ አቀራረብህን፣ ሁሉ ነገርህን ትረሳለህ። እንዳለመታደል ግን ፊት ለፊትህ የቆመዉ ሰዉ እንዳንተ ራሱን የረሳ ቢሆንም ያንተ ሁኔታ ግን ይመለከተዋል። ምን እንደለበስክ፥ ምን እንደተናገርክ፣ ምን እየተሰማህ እንደሆነ ሁሉ ያዉቃል። ፍላጎቱ ሁሉ አንተ ነህ። አንተም እሱን፥ እሱም አንተን በመገምገም ህይወት ያልፋል። በመሃከል ፍፁም ትኩረት የሚገባዉና ልታሳድገዉ የምትፈልገዉ አንድ ሰዉ ይረሳል። ይህ ነገር የሆነ ጊዜ ላይ መቆም አለበት። እንደግለሰብ ራሳችንን ልንመለከት ይገባል። እያንዳንዱን ነገራችንን ልናዉቀዉና ዛሬ ካለበት የነቀዘ ማንነት ልናወጣዉ ይገባል። ለራሳችን ተገቢዉን ክብር ልንሰጥ ይገባል። እንደሰዉ ራሳችንን ከሚያዋርድና ክብራችንን ከሚነካ ነገር መራቅ አለብን። ከሰዎች ምንም አይነት ዉዳሴ ሳንጠብቅ መልካም የሆነዉንና ተገቢዉን ነገር ብቻ እየሰራን ወደፊት መጓዝ አለብን። ከሰዎች ህይወት እንዉጣ። ስለሌሎች ሰዎች የግል ህይወትና ስኬት ከሚያወሩ ጓዳዮች እንራቅ። እስከሚገባኝ ድረስ የእኔ ወይንም ያንተ የግል ህይወት ለሌላ ሰው ያንን ያህል ለዉጥ አያመጥም። ለዉጥ የሚያመጣዉ ያንተ መለወጥ ነዉ። ያ ደግሞ እጅግ የሰከነና የማይቋረጥ ትኩረት ይፈልጋል። ራስህን በረሳኸዉ ቁጥር ማንነትህ የተለመደና አሰልቺ ይሆናል። ሰዎች የሚገባህን ክብር አይሰጡህም። ለሚወዱህ ሰዎች የልብ ስብራት ትሆናለህ። ካንተ የበለጠ እነሱ ላንተ መጨነቅ ይጀምራሉ። መቸ ነዉ እንደትልቅ ሰዉ የሚያስበዉ? መቸ ነዉ ሰዎች አክብረዉ የሚያናግሩት? መቸ ነዉ ማህበረሰቡ ትልቅ አደራ የሚጥልበት ሰዉ የሚሆነዉ? መቸ ነዉ ችግር በመጣ ቁጥር እርዳታ ፍለጋ መሮጡን ትቶ በልበ ሙሉነት ራሱን ችሎ የሚቆመዉ እያሉ ይጨነቃሉ? ምክንያቱም አንተ ራስክን ብትረሳም ራሳቸዉን የረሱት ግን አይረሱህም። እነሱ እየወደቁ እንኳ ያንተ ዉድቀት ምን እንደሚመስል ለማየት የሚጣጣሩ አሉ። የሚወዱህ ሊያግዙህ ይሞክራሉ። ግን እስከመቸ? እንኳን በስጋ ያልተዛመደ የእናት ሆድም ቢሆን እኮ ሙሉ ጤና ይዞ ራሱን በረሳ ልጅ ሁሌም ልቧ እንዳዘነ ነዉ። እናም ወንድሜ! ራስክን አትርሳ። ስለሰዉ ለማወቅ ለመጣርና በማይረቡ ወሬዎች ጊዜን ከማጥፋት የሆነ ትምህርት ተማር። ብዙ ሰዉ ታዉቃለህ። ራስህን የበለጠ እንድታዉቅ የሚያደርጉ መፃህፍትን አንብብ። አንተ ለራስህ ምርጥ ሰው ሆነህ ከተገኘህ ይህ ከራስ አልፎ ሀገር ይገነባል። የምታዉቃቸዉ ታላላቅ ሰዎች እዚህ የደረሱት ስላንተ በማሰብ አይደለም። ሃሳባቸዉ ሁሉ እንዴት ራሳቸዉን የተሻሉ ሰዎች ማድረግ እንዳለባቸዉ ነዉ። የምለዉን ካላመንከኝ እስኪ ለተወሰኑ ሳምንታት ራስህን የትኩረት ማእከል አድርገህ ተንቀሳቀስ። በሁሉም የህይወት ክፍል ዉስጥ ልታሻሽለዉ የምትችለዉ ነገር ይኖራል። አለባበስህ፥ ንግግርህ፥ እርምጃህ፥ ምስጋናህ፥ ግንኙነትህ፥ ሰላምታህ፥ ፈገግታህ፥ ምላሽህ፥ ድምፅህ፥ የማንበብ ባህልህ፥ ርጋታህ፥ ጓደኞችህ፥ ልማድህ፥ ሳቅህ፥ ስራህ፥ የመኖሪያ ቦታህ፥ መልክህ፥ ንፅህናህ...እመነኝ በጣም ብዙ ልታስተካክለዉ የምትችለዉ ነገር አለ። ስለሌላ ሰው እያሰበ ስኬት ላይ የደረሰ የለም! ለራስህ ትኩረት ስጥ!

ሰሞኑን የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና ወስደዉ በአሜሪካ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር እድል ያገኙት ታዳጊዎች ለእያንዳንዳችን ትልቅ ትምህርት ሰጥተዉን ይሄዳሉ ብየ አምናለሁ። ሁሌም ተማር። ሁሌም አንብብ። ሁሌም የተሻለ ቦታ ለመድረስ ለሚፈልግ ድሃ ህዝብ ያለዉ ብቸኛ ተስፋ ትምህርት ነዉ። ምንም ያህል ዉድ ይሁን። ምንም ያህል ትንሽ ይሁን። ምንም ያህል ደካማ ተማሪ ሁን። ከትምህርት ቤት ስትመለስ የተሻልክ ሰዉ ነዉ የምትሆነዉ። እነዚህ ታዳጊዎች ይህንን እናገኛለን ብለዉ አይደለም እረፍትና እንቅልፍ ጋር እየታገሉ እዚህ የደረሱት። ይብዛም ይነስም የትምህርት ፍሬ ትልቅ መሆኑን ያዉቃሉ። ስለዚህ የግል ትምህርት ቤት መጀመር ካለብህ ዛሬዉኑ ጀምር። ዉድ እንኳን ቢሆን መሞከር አለብህ። ያቋረጣችሁ ካላችሁ የማታም ቢሆን መጀመር አለባችሁ። ዲግሪ ያላችሁ ማስተርስ መማር አለባችሁ። ወይንም ሌላ በገበያ ላይ ይበልጥ ተፈላጊ የሆነ ትምህርት ተማሩ። አጫጭር ስልጠናዎችም በጣም ትልቅ ልዩነት ይፈጥራሉ። ትምህርት ትልቅ ሃይል ነዉ። እነዚህ ልጆች ካደረጉት አንተም በአቅምህ ልታደርገዉ የምትችለዉ ነገር ይኖራል። ስለእዉነት ትምህርት የማይለዉጠዉ ነገር የለም። ይህንን ለመረዳት ጊዜ በወሰደብህ ቁጥር ያለህን አቅም ይዘህ እየተኛህ ነዉ። ወደ ት/ቤት ተመለስ!

የግድ ልታነበዉ ይገባል ብየ አስባለሁ! ***+++*** አንዳንዴ በጣም ጥሩ፥ ጭዋ፥ ስነ ስርአት ያለዉ፥ ቀናና ሃይማኖተኛ ሰዉ እንሆንና ግን በዙሪያችን ርባና ያላቸዉ ሰዎች እናጣ ይሆናል። የበለጠ ጥሩ ለመሆን በሞከርን ቁጥር ደግሞ ይባስ ሰዎች አይተዉ ይሸሹናል። እንዲያዉም አንድ ሰዉ ከልክ በላይ በጣም ጥሩ ሲሆን ያስፈራል። ባስ ሲልም ያስጠረጥራል። በዚህ አለም ሰዉ እንዲሁ መልካም ሊሆን አይችልም። ካንተ የሆነ ነገር ካልፈለገ በስተቀር። ለዚያም ነዉ በጣም መልካም የሚባሉ ሰዎችን አድናቂ እንጂ ወዳጅ ሲያፈሩ የማናየዉ። በጣም መልካም ባህሪን ሁሉም ሰው ይፈልጋል። ወላጆቻችን፥ ሃይማኖታችን፥ መምህሮቻችን፥ ማህበረሰባችን ሁሉም መልካም ባህሪ ያለዉ ተተኪ ይፈልጋል። ምክንያቱም መልካም ሰዎች ፍፁም የሚያስቸግሩ ሰዎች አይደሉም። በቀላሉ ትለዉጣቸዋለህ። በፈለከዉ መንገድ ይከተሉሃል። እነሱን መምራት ቀላል ነዉ። ነገር ግን ወደግለሰብ ደረጃ ወረድ ብለን በተለምዶ በጣም መልካም የሚባሉ ሰዎችን ባህሪ ስንመለከተዉ በዉስጣቸዉ እጅግ በጣም ስር የሰደደ የመወደድ፥ የመደነቅና ይሁንታ የማግኘት ፍላጎት አለ። ከሚፈልጓቸዉ ሰዎች ይህንን ትኩረት ካላገኙ እስከመጨረሻዉ ጥግ ድረስ ለመሄድ የተዘጋጁ ናቸዉ። እየሰደቧቸዉ፥ እየረገጧቸዉ፥ ክብራቸዉን ሁሉ እስከመሸጥ ይደርሳሉ። ጥቅማቸዉን አሳልፈዉ ይሰጣሉ። ሰዎች ያለአግባብ እየጎዷቸዉ እንኳ ሆነ ብለዉ ምንም እንዳልተፈጠረ ያስመስላሉ። ትህትናቸዉና መሽቆጥቆጣቸዉ ከልክ በላይ ያቅለሸልሻል። ከላይ ሲታይ ይህንን የሚያደርጉት ለሰዉና ፈጣሪ ያላቸዉን ክብርና ፍቅር ለማሳየት ይመስላል። እዉነታዉ ግን እሱ አይደለም። ሰዎች ስለመልካምነታቸዉ እንዲወዷቸዉና እንዲያደንቋቸዉ ካላቸዉ ፅኑ ፍላጎት እንጂ። ችግሩ ግን ሰዎችን በመልካምነትህ ለማሸነፍ ስትል ብዙ ርቀት በተጓዝክ ቁጥር ራስህን እያጣኸዉና ከእዉነት መንገድ ወጥተህ ግብዝ እየሆንክ መሄድህ ነው። ይህን ማቆም አለብህ። መልካምነት ልክ አለዉ። ትህትና ልክ አለዉ። ሰዎችን ማስደሰት ልክ አለዉ። ለዚያም ነዉ ከሰዎች ክብርንና ፍቅርን ፍለጋ መልካም እየሆንክላቸዉ በሄድክ ቁጥር እነሱ ላንተ ያለቸዉ ፍቅርና ክብር የሚወርደዉ። ይህን ስል ጭራሽ መልካም ሰዉ መሆን መጥፎ ነዉ እያልኩ እንዳልሆነ ይገባሃል። የምልህ ያለዉ በጣም ሲበዛ መልካም ሰዉ መሆንህን ለማሳየት አትሞክር ነዉ። ከማንም ቢሆን ክብርና ፍቅር ጠብቀህ ስራ መስራትህን ተዉ። ማንም ስላንተ የሚያስበዉ ነገር ግድ አይስጥህ። ቅዱስ አትናቲዮስ ፓትርያርክ ከመንበሩ ተባሮ "አለሙ ሁሉ ጠልቶሃል!" ሲሉት እሱም "እኔም አለምን ጠልቸዋለሁ!" እንዳለዉ አይነት ህይወት እንኑር። ይህ በጣም ጥግ የያዘ ምሳሌ ይሆናል። ግን በዚህ ምድር በስኬት፥ በደስታና በልበ ሙሉነት መኖር ከፈለግን ሰዎች ስለእኛ ስለሚያስቡት ነገር መጨነቃችንን ማቆም አለብን። ጠ/ሚ ሃ/ማርያም ደሳለኝ ፌስቡክ ላይ ስለእሱ የሚወራዉን አሉባልታና አንቋሻሽ ወሬ ወደልቡ ቢያስገባዉ ኖሮ አይደለም አራት አመት ይቅርና አራት ወር እንኳ ስልጣን ላይ አይቆይም ነበር። እሱ ግን ማንም ምንም ቢል ግድ የለዉም። የሚያስፈልገን እንዲህ አይነት ስነልቦና ነው። ሰዎችን ለማስደሰት አንኑር። ደስታችንና ስሜታችን ሌሎች ሰዎች ድርጊት ላይ እንዳይንጠለጠል እናድርግ። ምናልባትም እንደአስቴር "ስለሰዉ ስለሰዉ ቀድጀ ልልበሰዉ!" ማለት ካለብንም እናድርገዉ። ስለሰዎች አድናቆት፥ ክብርና ፍቅር መኖራችንን እናቁም። መሄድ ካለብህ ሌሎች በፈለጉትና በተመቻቸዉ መንገድ ሳይሆን አንተ በወደድከዉና ባመንከዉ ጎዳና ላይ ነዉ። መልካም ሰዉ መሆንህን ለማሳየት በአነጋገርህ፥ በአረማመድህ፥ በአለባበስህ ላይ ያልተገባና የተጋነነ ለዉጥ አድርገህ ከሆነ ራስህ ፈትሽ። በጊዜ ሂደት ሰዎች በሙሉ እንደነጭ አንሶላ እንዳያቆሽሹህ ፈርተዉ ተራ በተራ ጥለዉህ ነዉ የሚሄዱ። ሰዎችን ከልክ ባለፈ ትህትናና ጭዋነት ለመሳብና ለመመሰጥ የምናደርገዉ ልፋት በስተመጨረሻ የአድናቆትና የጭብጨባ እስረኛ ነዉ የሚያደርገን!

የበግ ግልገል በሜዳ ሲዘል ስታየዉ በጣም ደስ ይላል። ዝንጀሮ በቁጥኙ ሲፈነጭ ስታየዉ ያስገርማል። ከድንጋይ ወደ ድንጋይ፥ ከገደል ወደገደል ሲወረወር ወድቆ መፈጥፈጥ የሚለዉ ነገር አይታየዉም። አሳ በማእበል ዉስጥ ያለምንም ፍርሃትና ችግር እድሜ ልኩን እየዋኘ ይኖራል። ሙቀትና ብርድ የሚያሸንፉት አይመስሉም። ታዲያ በግ በበግነቱ፥ ዝንጀሮም በዝንጀሮነቱ፥ አሳም በአሳነቱ ሲያፍር አናያም። ምክንያቱም ሁሉም ባላቸዉ ህይወት ደስተኞች ናቸዉ። ማናቸዉም ስለማናቸዉም አስበዉ አያዉቁም። ደስታ ከፈለግህ እንደዚህ ማሰብ አለብህ። ስኬት ከፈለግህ ራስህን ከማይረባ ንፅፅር ማዉጣት አለብህ። በቋንቋህ፥ በቆዳ ቀለምህ፥ በአለባበስህ፥ በድህነትህ፥ በሃይማኖትህ፥ በባህልህ በፍፁም ልታፍር አይገባም። ምክንያቱም የሚያምርብህ ምንም ባልተበረዘው ማንነትህ ዉስጥ ስትሆን ነዉ። ቀልድህ የሚያምረዉ በቋንቋህ ሲሆን ነዉ። ቀልድህ የሚገባቸዉ ያንተ የሆኑት ሰዎች ብቻ ናቸዉ። ስለዚህ ራስህን ከንፅፅር አለም አዉጣ። ነጮች የተሻለ ቦታ ላይ ቢገኙ ያ አንተን አይመለከትም። ሙስሊሞችና አይሁዶች ለንግድ የተፈጠረ ባህሪ ቢኖራቸዉ ይህ አንተን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም። ወይንም የጓደኞችህ የተለየ የቋንቋ ችሎታ ካንተ ጋር የሚያገናኘዉ ነገር የለም። አንተ የራስህ አለም አለህ። ከአባቶች የወረስከዉ ሃይማኖትና ትዉፊት አለህ። እስከነድክመትህ በምንም ነገር ሊለዉጡህ የማይችሉ ወላጆች አሉህ። ለማን ደስ ይበል ብለህ ህሊናህ የማይፈቅደዉንና የማይመችህን ነገር ታደርጋለህ? ለሰዉ ደስ ይበል ብለህ ባህር ዉስጥ ትኖራለህ? ከዝንጀሮዎች ጋር ለመመሳሰል ገደል ለገደል ትሄዳለህ? አይ። እንደሱ ጥሩ አይደለም ወንድሜ። እንኳን ላንተ ምንም ግድ ለማይሰጠው አልፎ ሂያጅ ይቅርና በጣም ለምትወደዉና ለምታከብረዉ ሰዉ እንኳ ቢሆን ማንነትህና ስብእናህን ለድርድር የማታቀርብ ሰዉ መሆንህን ማሳየት የሚኖርብህ ጊዜ ይኖራል። ለጋ ተፈጥሮ ይዘን የትም አንዘልቅም። ማንም እንደፈለገ የሚመራዉ የመስኖ ዉሃ መሆን የለብንም። ለሰዎች የግል አስተያየት፥ ፍላጎትና እምነት ሰለባዎች ከመሆን ራሳችንን መጠበቅ አለብን። ዛሬ የተሻለ ቦታ ላይ ስላሉ ብቻ የግድ እነሱን መምሰልና መከተል እንዳለብን ማሰባችንን ማቆም አለብን። ሃብታቸዉም፥ ዝናቸዉም፥ ስልጣኔያቸዉም፥ መልካቸዉም፥ ስራቸዉም ለእኛ አንዳች በጎ ነገር ለማያመጣ ሰዎች ራሳችንን ባሪያ አድርገን ማቅረብ የለብንም። በስራቸዉ ያሸነፉን ሰዎች ቢሆኑ እንኳ የእነሱ አጨብጫቢዎች ሳይሆን የፍሬያቸዉ ተከታዮች ነዉ መሆን ያለብን። እንደሰዉ ሳይሆን እንደግለሰብ እንኑር። ሌሎች ስላደረጉት ብቻ ህሊና የማይፈቅደውንና ልብ ያላረፈበትን ነገር ማድረግ ማቆም አለብን። ባለንበት እንደሰት። በማንነታችን አንፈር። የማንፈልገዉንና የማይመቸንን፥ ያላመንበትና የማይመለከተንን ነገር በልበ ሙሉነት "አይሆንም!" እንበል። ዝንጀሮዎች ከሆንን እንደዝንጀሮ እንኖራለን። እነሱ እንደባህላቸዉ ይደጉ። እኛ ደግሞ እንደኢትዮጵያዊ እናድጋለን። በዚህ ልናፍር አይገባም። ድሃ መሆናችን ማንነታችንን እንድንቀይ ሊያደርገን አይገባም። ድሃ ነን። ኩሩዎችም ነን። ከዚህ ላይ መጨመር ያለብን ነገር እጅና እግርን ማንቀሳቀስ ብቻ ነዉ። ሁሉቱ ከተንቀሳቀሱ ሆድ ፆሙን አያድርም። ስለዚህ እንደግለሰብ አንተ ራስህን ከሌሎች ጋር ማነፃፀር አቁም። ቋንቋህን፥ ቀለምህን፥ ዘርህን፥ ሃይማኖትህን፥ የኑሮ ሁኔታህን መሰረት አድርገህ ለራስህ ደረጃ አታዉጣ። የትም ብትሄድ ደረጃና ደረጃ መዳቢዎች ይኖራሉ። ያለዉ ብቸኛና ትክክለኛ አማራጭ ራስን የሌሎችን ጨዋታ ከመጫወት ማግለል ነዉ። ከራስህ ሜዳ ከወጣህ ሁሌም ተሸናፊ ነህ። ይህንን አትፍቀድ። በማንነትህ ልታፍር አይገባም። ሁላችንም ድሃዎችና ቁምጣ ለባሾች ሆነን ነዉ ያደግነዉ። ጎጃም አዘነ ለብሰን ነዉ የተማርነዉ። ይህ ግን የምንኮራበት የማንነታችን አካል እንጂ የምናፍርበት ስድብ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድህነት ምን እንደሆነ ያዉቃል። የታደሉት ጥቂቶቹ እንኳ ቢሆኑ በወዳጅ ዘመዶቻቸዉ ላይ ደርሶ ያዩታል። በዚህ ልናፍር አይገባም። ማፈር ካለብን በስንፍናችን እንፈር። ማፈር ካለብን ተቀምጠን ዉለን ተኝተን በማደራችን እንፈር። ማፈር ካለብን በሃያ አምስት አመታችን በወላጆቻችን ድጎማ ላይ በመኖራችን እንፈር። ማፈር ካለብን ስራ በመምረጣችን እንፈር። ማፈር ካለብን በሱሰኝነታችን እንፈር። በከንቱ ዘመናዊነታችን እንፈር። በብልግናችን እንፈር። በዘረኝነታችን እንፈር። ማፈር ካለብን በነዚህ ነገሮች እንፈር እንጂ አባቶቻችንን ባወረሱን ማንነትና የህይወት መንገዶችማ ልናፍር አይገባም። እናም ሌሎች እንደሃገራቸው እንዲቀድሱ ተዋቸዉ። አንተም እንደሃገርህ ቀድስ። እነሱም እንደፈለጉት ይኑሩ። አንተም በፈጣሪ፥ በአባቶችና በህሊናህ ዘንድ ምንም አይነት ወቀሳ በሌለበት የህይወት አለም ኑር። በማንነትህ አትፈር።


Purchase this book or download sample versions for your ebook reader.
(Pages 1-13 show above.)